ባለፉት አመታት በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በዞናችን በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል፦አቶ ዘይኔ ቢልካ
ባለፉት አመታት በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በዞናችን በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል፦አቶ ዘይኔ ቢልካ
ወራቤ፣የካቲት 20/2018
የስልጤ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቤት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክትና ማኒፌስቶ ማስተዋወቂያ መርሃ-ግብር ተካሄዷል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ ባለፉት አመታት በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በዞናችን በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የለውጡ መንግስት የህዝብን ጥያቄ በቅደም ተከተል እየፈታ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በመደመር መንግስት ጠንካራ ስልጤን እና ኢትዮጵያን እንፈጥራለን ብለዋል።
ብልፅግናን መምረጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል ነውም ብለዋል።
የሀሰብ የበላይነት ኢትዮጲያን ያሻግራል ያሉት አቶ ዘይኔ በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲሳካ መጣር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ብልፅግና የዴሞክራሲ ስብራቶችን በመጠገን
ሁሉም በሃሳብ የሚሳተፍበትን ሜዳ ፈጥሯል ያሉት አቶ ዘይኔ በሁሉም ዘርፎች እምርታዊ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ለህዝብ ቃል የገባቸው ሰፊ ስራዎችን በመፈፀም የህዝብ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ይገኛል ብልዋል።
በብልፅግና ፓርቲ አመራር ሰጪነት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የህዝብ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ መፍታት የብልፅግና ፓርቲ መለያ መገለጫ ሆኗል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ዞኑን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ስራ መሰራቱንም አብራርተዋል።
ብልፅግና ለግለሰብ እና ለቡድን መብቶች እኩል እውቅናና ትኩረት ይሰጣል ያሉት አቶ ዘይኔ በሁሉም ለሁሉም የምትሆን ሀገር ለመገንባት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ።
ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና አሳታፊ እንዲሆን የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባሎች አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የስልጤ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ፅ ቤት ኃላፊ እና የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ ነዒማ ሙኒር በበኩላቸው ብልፅግና ፓርቲ ለትውልዱ እዳ ሳይሆን ምንዳ የሚያወርስ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ፓርቲው ባለፉት አምስት አመታት በሀገራችን እንዲሁም በዞናችን ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡንም ገልፀዋል።
ባለፉት አመታት የህዝባችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው ያሉት ሀላፊዋ የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ላይ ሀብት የፈጠሩ ወጣቶችን መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
እንደ ዞን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ላይ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አንስተው በመንገድ በውኃ በመብራት ላይ ሰፊ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በማህበራዊ ዘርፍም የጤና ተቋማት ግንባታ እንዲሁም የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽነትን ማስፋፋት ላይ የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን ወይዘሮ ነኢማ አብራርተዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ሶስት ትልሞችን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለው አንደኛ ሰብኣዊ ልእልና ማረጋገጥ ሁለተኛ የኢኮኖሚ ልዋላዊነት ማረጋገጥ እና ሶስተኛ አፍሪካዊት ሀያል ሀገር መፍጠርን ይተልማል ብለዋል።
በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሁለት የምርጫ ግቦች ማለትም ምርጫው ፍትሃዊ እንዲሆን ማስቻል እና ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው ማሸነፍ እንዲችል የፓርቲ አባላቱ በትኩረት መስራት ኣለባቸው ብለዋል።
ብልፅግና በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተግባር ተፈትሾ በተረጋገጠ ውጤት የሚወዳደር ፓርቲ መሆኑንም ወ/ሮ ነዒማ ገልፀዋል።
ትላንትናን በማከም ነገን በመተለም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚሰራ ፓርቲ መሆኑንም ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ዞናችንን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ባለፉት ዓመታት ለህዝቡ ከተገቡ ቃሎች በርካቶችን ማሳካት መቻሉንም ወ/ሮ ነዒማ ሙኒር አስታውቀዋል።